(ውሃ የበላው ኣርፋ ይይዛል)
(የኦነግ መግለጫ)
የመንግስት የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሊታወጅ ይችላል። መንግስታት የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅን የሚያውጁት በሃገሪቷና በሃገሪቷ ህዝቦች ላይ የተለየ ሁኔታ ሲፈጥርና ኣደጋ ያስከትላል የሚል ስጋት ሲኖራቸው ነው። እንዲህ ያለው ለህዝብና ለሃገር ከመቆርቆር የሚታወጅ ኣዋጅ በዲሞክራሲያዊ መንግስታት ስር ይታያል። ጥቅምት 9 ቀን 2016ዓም የታወጀው የወያኔ የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ግን የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦችን ከኣደጋ ለማታደግ ሳይሆን ወያኔ/ሕወሃትን ከወድቀት በማዳን እድሜውን ለማራዘም የታወጀ ነው።
የወያኔ/ሕወሃት መንግስት ጥቅምት 9 ቀን 2016ዓም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላለፈው የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይጸድቅ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ታውጇል። ይህ የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ የመጀመሪያው ኣይደለም። በ1992ዓም ተመሳሳይ ኣዋጅ በወቅቱ ፕሬዝዳንት መለስ ዜናዊ ታውጆ የኦሮሞ ዜጎች በየቦታው ሲገደሉና ሲታሰሩ ነበር። በዚህ ኣዋጅ ምክንያት ከህጻናት እስከ ኣዛውንት ያሉ በኣስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ዜጎች በሁርሶና ዲዴሳ እስር ቤቶች በመታሰራቸው የኣያሌ ዜጎች ህይወት ኣልፏል። በርካታ የኦሮሞ ዜጎች ደግሞ በነዚሁ እስር ቤቶች ውስጥ በወያኔ ለሰቆቃ በመዳረጋቸው ለኣካለ-ስንኩልነት መዳረጋቸውን የኦሮሞ ህዝብ ዛሬም ያስታውሳል።
ጥቅምት 9 ቀን 2016ዓም የታወጀው ኣዋጅ እየተካሄደ ያለውን ኣስከፊ ሁኔታ ይበልጥ ግልጽ ከማድረግ በተረፈ የኦሮሞ ህዝብ ላለፉት 25 ዓመታት ተመሳሳይ ኣዋጅ ስር ስለነበር ኣዲስ ኣይሆንበትም ማለት ይቻላል። የኦሮሞ ህዝብ ከካድሬዎችና የቀበሌ ሚሊሻዎች እስከ ከፍተኛ ሹማምንት በተሰጠ ትዕዛዝ ሲታሰር፣ ሲሰደድና ሲገደል ነበር። በግድያና እስራት ኣስፈራቶ የኦሮሞን ህዝብ በቁጥጥር ስር በማስገባት የኣምባገነናዊ ስርዓትን ለማስቀጠል በኦሮሚያ ስራ ላይ እየዋለ ያለው በወያኔ ቡድን በሚመራው ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ካሁን ቀደም ታህሳስ 15/16 ቀን 2016ዓም በሃይለማሪያም ደሳለኝና በጌታቸው ረዳ ታውጇል። በተጨማሪም ኦሮሚያን በ8 ቀጣናዎች በመከፋፈል በወታደራዊ ኣስተዳደር ስር በማስገባት ያሻቸውን እርምጃ ሲወስዱ ዛሬ ደርሰዋል።
ዲሞክራሲያዊ መንግስታት የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ የሚያውጁት በሃገርና በህዝብ ላይ የሚደርስን ኣደጋ ለመቆጣጠርና ለማሳነስ ሲባል ነው። ወያኔ ግን የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ያወጀው በሃገርና በህዝብ ላይ ኣደጋ ይደርሳል ብሎ በማሰብ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ሲካሄድ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ በሃይል የተቆጣጠረው ስልጣን ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ ነው። ስለሆነም ይህ የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ወያኔን ስልጣን ላይ ለማቆየት የወጣ ነው። በዚህም በሃገሪቷ ህዝቦች ላይ ያሻቸውን እርምጃ ለመውሰድ ይገለገሉበታል። የጭካኔ ግድያና እስራትን በስፋት በማካሄድ እድሜውን ለማራዘም ይጠቀምበታል። ሃሳብን በነጻነት መግለጽ፣ መሰባሰብ፣ በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ድምጽ ማሰማትና ሌሎችም መሰረታዊ መብቶች በዚህ ኣዋጅ ገደብ የሚጣልባቸው ይሆናል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች እስከ ዛሬ የኖሩት በኣናሳ ቡድን ኣገዛዝ ስር እየተገደሉ፣ እየታሰሩና የከፋ ጭቆና እየደረሰባቸው እንጂ እንደዜጋ በህግና በተፈጥሮ ያሏቸው መብቶች ተከብሮላቸው ኣይደለም። በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ለዚህ መንግስት ፍጻሜ ማበጀት ኣለብኝ ብሎ በኣንድነት በመነሳት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን እያፋፋመ ያለው ጭቆና ስለበረታበት ነው። በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ ዛሬም ቢሆን ይህን ርህራሄ የሌለውን መንግስት ከላዩ ላይ ለማሽቀንጠር መታገል መብቱ ነው። ይህንን መብቱን ለመገደብ በኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ስም የታወጀበትን ዘመቻ ለመቀልበስም ሙሉ መብት ኣለው።
ስለዚህ ለኦሮሞ ነጻነት ትግል እንዲሁም ለእርስበርሱ የገባውን ቃል በማክበር ለዚህ መንግስት ፍጻሜ ለማበጀት ፍልሚያውን እንዲያፋፍም ኦነግ ያውጃል። ከዚሁ ጋር ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ፋሽስቱን የወያኔ መንግስት ማስወገድ ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ የሚተው ጉዳይ እንዳልሆነ ተገንዝበው የዜጎች ሰላም፣ ዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት እንዲከበርና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚታገሉ ሁሉ ይህንን በጭካኔ በህዝቡ ላይ የታወጀውን የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ለማክሸፍና ይህንን መንስግት ለማስወገድ በጋራ እንዲንቀሳቀሱ ሁሉንም ህዝቦች ኣጥብቀን እናሳስባለን።
ድል ለኦሮሞ ህዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ጥቅምት 10 ቀን 2016ዓም