ሠይፉ አደም | May 12, 2016
በአገራችን ዘላልነት ወቅቶችን ተከትለው ከሚመጣው የኑሮ ዘይቤ(lifestyle) ማለት ነው። በተለይ በቆላና ዝናብ አጠር በሆኑ አከባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ለከብቶቻቸው ሳርና ውሃን ፍለጋ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት ቋሚ የመኖሪያ ቦታ ስለሌላቸው ዘላን ይባላሉ። ዘላኖች ለከብቶቻቸው ክብርና ፍቅር አላቸው። በዚህም የተነሳ በበጋ ጊዜ ሳርና ውሃ ፍለጋ የዱር እንስሳት ብቻ ወደሚኖሩበት ጫካ ድረስ በመዝለቅ ከጅብ፤ አንበሳ፤ አዞ፤ ዘንዶና ከመሳሰሉት አደገኛ አውሬዎች ጋር የፋለማሉ። በዚህም ህይወታቸውን የሚያጡትን የዘላኖች ቁጥር ከፈጣሪ በስተቀር ማን ያውቃል?
ይህ እንደ መግቢያ ያነሳሁት ሀሳብ በዘላኖች የኑሮ ሁኔታ ላይ ለማትኮር ሳይሆን የኦሮሞ አርቲስቶች የኑሮ ሁኔታ ከዘላኖች የኑሮ ሁኔታ ጋር ያለውን ተመሳይነት ለማሳየት ነው።
የኦሮሞ አርቲስቶች ጎበዞችና ቆራጦች ናቸው። የማህበረሰባቸው እሮሮ እና ጭቆና ያሳስባቸዋል። የኦሮሞ ህዝብ ነፃነቱን ለመጎናጸፍ በሚያደርገው ትግል ውስጥ ከድሮ ጀምረው እስከ አሁን ዋናውን ሚና በመጨወት ለይ ይገኛሉ። የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ተከትለው በተቀሰቀሰው የኦሮሞ ህዝብ ነቅናቄ (#OromoProtests) በነበሩት አራት እና አምስት ወራት ውስጥ እንኳ ንቅናቄውን የተመለከቱ ከ200 በለይ ዘፈኖችን ዘፍነዋል። ይህ በኢትዮጲያ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ይህ ሙያ፣ አቅምና ቆራጥነት የታያበት ሥራቸው ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ ያኮረዋል።
አዎ፤ የኦሮሞ አርቲስቶች ሥራ ያስደስታል። ግን ለዚህ ሙያቸው የሚከፍሉት መስወዕትነት ደግሞ በጣም የበዛ ነው። ብዙዎቹ ብርቅዬ አርቲስቶች ለኦሮሞ ህዝብ ንፃነት ብለው ህይወታችውን አጥተዋል፤ ብዙዎቹ ታስረዋል፤ ብዙዎች ደግሞ ከነአካቴው ደብዛቸው ጠፍተዋል። ይህ መሆኑ ያሳዝናል!
ያልሞቱትና ደብዛቸው ያልጠፈው የኦሮሞ አርቲስቶች ደግሞ እስኪሞቱና ደብዛቸው እስኪጠፋ ድረስ የዘላኖችን ኑሮ ይኖራሉ። በቆላና ዝናብ አጠር በሆኑ አከባቢዎች እንደሚኖሩ አርቢቶ አደሮች ሳይሆን መሃል አዲስ አበባ ውስጥ ዘላን ሆነው ይኖራሉ። አርቢቶ አደሮቹ አንድ ቦታ መኖር እንደማይችሉ ሁሉ አርቲስቶቹም አድስ አበባ ውስጥ አንድ ቤትና አንድ ሰፈር ውስጥ መኖር አይችሉም። ግን በዘላን አርቢቶ አደሮችና በአርቲስቶቻችን መሃል ትልቅ ልዩነት አለ። ዘላኖቹ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱት ሳርና ውሃ ፍለጋ ሲሆን አርቲስቶቻችን ግን ቦታ የሚለዋውጡት እነሱን ለማስፈራራት፥ ለመግረፍና ለማሰር የሚፈልጉትን ባለጊዜዎችን ለመሸሽ ነው። ብዙዎቹ አንድ ቤትና አንድ ሰፍር ውስጥ ከአምስትና ስድስት ወራት በላይ መኖር አይችሉም። ስለዚህ ቦታ ለቀው ወደ ሌላ ቤት ወደ ሌላ ሰፈር ይሰደዳሉ። ብዙዎቹ ትዳር ያላቸው አርቲስቶች ‘አሳሪዎቹ ሌሊት መጥተው ከቤት ውስደው ያስሩናል’ በሚል ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን/ባሎቻቸውን ጥለው ውጭ ያድራሉ። ትዳር የሌላቸው አርቲስቶቻችን ደግሞ ለብቻቸው ቤት ለመከራየት በቂ ገንዘብ ስለሌላቸው (የሙዚቃ ኮንሰርት አዘጋጅተው ገንዘብ እንዲያገኙ አይፈቀድላቸውም)በቡድን ሆነው ስለሚከራዩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አከራዮቻቸው ‘ቤት ታበላሻላሽሁ ወይ ግንዘብ ጨምሩ ወይ ውጡ’ ሲለሚሏቸው አሁንም ወደ ሌላ ሰፈር ለመሰደድ ይገደዳሉ። አንዳንዴም ቤት አከራዮች በካድሬዎች ግፊት የተነሳ ተከራዮች ቤታቸውን ለቆላቸው እንዲወጡ ያስገድዳሉ።
በአጠቃላይ የአርቲስቶቻችን ኑሮ ሁኔታ የዘላኖች ኑሮ ነው። መብት የለም፤ ቤት የለም፤ ገንዘብ የለም፤ ምንም የለም።አዎ ኑሯቸው አሳዛኝ የሰባራ ዝንጀሮ ኑሮ አይነት ነው:: ሰባራ ዝንጀሮ እሱ ወጌሻ ዘንድ አይሄድም ወጌሻም እሱ ጋ አይመጣም:: ፈጣሪ ያዳነው ቀን ብቻ ይድናል:: ይህ መሆኑ በጣም ያሳዝናል።
ነገር ግን አርቲስቶቻችን ይህን መዓት ሁሉ ችለው በለመሰልቸትና ተስፋ በለመቁረጥ በግምባር ቀደምትነት የኦሮሞን ትግል በመምራት ላይ ይገኛሉ። አዎ፤ እነሱ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነጌም ኩራታችን ናቸው። ሁሉም በእሳት ተፍትነው ያለፉ ወርቆቻችን ናቸው። እነዚህ ጌጦቻችን መዘከር፣ መከበር እና መበረታት አለባቸው። ካሴቶቻቸውንና ሲዲያቸውን ገዝተን ዘፈኖቻቸውን ማዳመጥ ያስፈልጋል። ምናልባትም በአመት ውስጥ ብዙ ቀናቶች አሉንና አንዱን ቀን ‘የአርት ቀን’ ወይም ሌላ ስያሜም ቢሆን ሰጥተነው አርቲስቶቻችን የሚንዘክርበት ቀን ቢኖረንስ?