(ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ) የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ከፍተኛ አመራር አባይ ጸሃዬ፤ ሳሞራ የኑስን ጨምረው ሌሎች ከፍተኛ የህወሃት ባልደረቦቻቸውንና በመያዝ አሜሪካ አገር አጭር ቆይታ አድርገው መመለሳቸውን ጎልጉል አረጋግጧል። አሜሪካ በግል የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማነጋገር ውሉ ባግባቡ የማይታወቅ የሽግግር ሃሳብ ለመተግበር ማሰቧ ተሰምቷል። የሽግግር ሃሳቡ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) የያዘውን ስልጣን በተወሰነ መልኩ የሚያስቀጥል በመሆኑ ለአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ሃሳብ የሚያቀርቡ ተጽእኖ ፈጣሪዎች አሜሪካ ይህንን መሰሉን አቋም እንድትቀይር እየወተወቱ ነው። ለኦባማ አስተዳደር ፖሊሲ አውጪዎች ዕቅድ ለማቅረብ እነዚሁ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዝግጅት አላቸው።
ከሁለት ቀን በፊት አሜሪካ አጭር ቆይታ ያደረጉት እነ አባይ ጸሃዬ “እንወድቃለን” ብለው እንደሚሰጉ ለአለቆቻቸው አስታውቀዋል። የጎልጉልየዲፕሎማት ምንጮች እንዳሉት ህወሃቶች አሁን የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ምን አልባትም ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥራቸው ሊወጣ እንደሚችል፣ ከተቃውሞው ጀርባ ያሉት ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ በቀጣይ ህዝብ የራሱን ነጻ አስተዳደር እንዲመሰርት እቅድ መያዛቸውን፣ የመንግስት መዋቅር እየፈረሰና ተቃዋሚዎች ከጀርባ ሆነው የሚመሩት ነጻ ክልል እየበዛ ሲሄድ ጽንፈኛው አይሲስ አገሪቱን ሊቆጣጠር ይችላል ሲሉ የአሜሪካ ሹሞችን ማስጠንቀቃቸው ተነግሯል። ሁለተኛ አማራጫቸውም ሙሉ በሙሉ ወደ ቻይና መጣበቅ ሊሆን እንደሚችል የህወሃት መሪዎች በማስፈራሪያ መልክ ፍንጭ ሰጥተዋል። ቻይና ግን ከፖለቲካ የበላይነት ይልቅ የኢኮኖሚ ጥቅሟን የምታስቀድም በመሆኗ ይህ የህወሃት “ማስፈራሪያ” ምን ያህል ሊሠራ እንደሚችል ለህወሃት ሹሞችም ግልጽ የሆነ አይመስልም፡፡
በ1997 ምርጫ ህወሃት ተሸንፎ ስለነበር ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲያደርግ አሜሪካኖቹ ሲጠይቁት መለስ “ሠራዊቴን በመያዝ ወደ ትግራይ አፈገፍጋለሁ፤ አገሪቱ የአሸባሪ መናኽሪያ ትሆናለች፣ ትፈራርሳለች፤ ተቃዋሚዎች ሃይል የላቸውም…” በማለት አስጠንቀቀው የአሜሪካንን ሃሳብ ካስቀየሩ በኋላ ወደ ግድያ መዛወራቸውና ድምጻቸው እንዲከበርላቸው የጠየቁ ንጹሃንን በአልሞ ተኳሾች እንዲገደሉ ቀጥተኛ ትዕዛዝ መስጠታቸው የሚታወስ ነው። መለስ ከአሜሪካኖቹ ጋር ያደረጉትን ድርድር በወቅቱ የወጣ ዓለምአቀፍ ሚዲያ ዘግቦት ነበር።
ዛሬ 25 ዓመት ራሱን ተገንጣይ በማለት ሰይሞ አገር በነጻ አውጪ ስም የሚገዛው ህወሃት፤ በተመሳሳይ የማስፈራራት ልምምዱን አንድ ደረጃ በማሳደግ “እኔ ከሌለሁ አገሪቱን አይሲስ ይወራታል” ሲል በወኪሎቹ አማካይነት አሜሪካ የሕዝቡን ተቃውሞው በጥገና ለውጥ እንድታፋዝዝላቸው ጠይቀዋል። እስረኞችን ለመፍታት፣ የሚዲያ ነጻነትን ለማወጅ፣ በቀጣዩ ምርጫ ተቃዋሚዎች ፓርላማ እንዲገቡ ለመፍቀድና የመሳሰሉትን ማሻሻያዎች እንደሚያከናውን ማረጋገጡን የዜናው አቀባዮች አመላክተዋል። ዴሞክራሲ ሂደት ነው፤ ስለዚህ በዚህ መልኩ በቀስታ እየተለካ ከተሰጠ ይበቃል በሚል ዓይነት ህወሃቶችን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ ጥገናዊ ለውጥ እንዲካሄድ ህወሃት ማስፈራሪ፣ ምልጃና ጭንቀት የወጠረው ጥያቄና ውትወታ ማቅረቡ ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል፡፡
እንደ ዜናው ሰዎች ገለጻ ከሆነ፣ ለአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አውጪዎች የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርቡት ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት ይህንን ሃሳብ አልተቀበሉትም። ምክንያታቸውም ወያኔዎች ሲጨንቃቸው የሚገቡትን ቃል የመተግበር ልማድ የሌላቸውና የማይታመኑ በመሆናቸው ነው። እነዚህ ክፍሎች አነሰ ቢባል በሳምንቱ ማብቂያ አገሪቱ ላይ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት የሚያስገድድ የውሳኔ ረቂቅ ሃሳብ ያቀርባሉ ተብሎ ይገመታል። የኦባማ አስተዳደርም የስራ ጊዜውን ሳያጠናቅቅ ይህንን ጉዳይ በጥልቀት እንዲመለከተው እንደሚወተውቱ ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ ተመሳሳይ ዜና ህወሃት ለጊዜውም ቢሆን ከመንበሩ እንዲነሳ የማትመኘው አሜሪካ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አመራሮች በግል ለማነጋገር መጋበዟ ታውቋል። በተለያዩ መለያዎች የሚታወቁትን የኦሮሞ ድርጅቶች ለማነጋገርና ወደ ድርድር ሲቀርቡ አንድ ቅርጽ እንዲይዙ ለማድረግ ማሰቧ ተደምጧል።
አንድ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር ለድርጅታቸው ከላይ የተጠቆመው አይነት ጥሪ መላኩን ለጎልጉል የአሜሪካ ዘጋቢ አረጋግጠዋል። የዚህ ጥሪ አካል ይሁን የሌላ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነትና የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መ/ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ራሳቸው በየፊናቸው ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ ክፍል (ECADF) የፓልቶክ መስኮት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት መረራ “አገሪቱ በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝ መክረናል” ሲሉ በሰለጠነ መንገድ አስቸኳይ ፖለቲካ መፈትሄ ሊፈለግ እንደሚገባ በመልሶቻቸው ወስጥ ሁሉ ሲያመላከቱ ተስተውሏል።
የሰማያዊ ፓርቲም መሪው ይልቃል ስላደረጉት ውይይት በፌስቡክ ገጹ ላይ አትቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ የመጣው የሕዝብ ተቃውሞ ለዓመታት የዘለቀ ግፍና መከራ ውጤት እንደሆነ የጠቀሱት ይልቃል፤ በአገዛዝ ላይ ያለው ኃይል ምንም ዓይነት ሕጋዊነት የሌለው በመሆኑ በሥልጣን ለመቆየት ባለፉት ዓመታት ሲያደርግ እንደቆየው መግደልና ማሰር እንደሚቀጥል ለአሜሪካውያኑ ሹሞች አስረድተዋል፡፡ አሜሪካ “የኢትዮጵያ ሁኔታ አሳስቦኛል” እያለች ለምታወጣው መግለጫ ሕዝቡ ምንም ግምት የማይሰጠው ደረጃ ላይ መድረሱን የተናገሩት ሊቀመንበር ይልቃል በማጭበርበር የተካነው ህወሃት ሥልጣን ላይ እያለ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ መካሄድ እንደማይቻል ፓርቲቸውም ሆነ ህዝቡ እንደማያምን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም “ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የማድረጊያው ብቸኛ መንገድ ጊዜያዊ ባለአደራ መንግሥት ማቋቋምና በአዲስ በሚመሠረተው የምርጫ ኮሚሽን ባስቸኳይ ብሔራዊ ምርጫ ማካሄድ ነው” ማለታቸውን የሰማያዊ ፓርቲ ዜና መግለጫ አስታውቋል፡፡
እነ አባይ ጸሃዬ የኦሮሞና የአማራ መተባበር እንዳሰጋቸው ለአሜሪካ ባለሥልጣናት አስረግጠው መናገራቸውን፣ የሁለቱ ብሔሮች መተባበርና አማራ ክልል ህዝብ ነፍጥ ማንሳቱ ደግሞ አሜሪካንን እጅግ እንዳሳሰባት የሚናገሩት ምንጮች፣ የህዝብ ተቃውሞ እያየለ ከሄደ የአሜሪካ ውሳኔ ሰጪ ኃይሎች ሃሳባቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ከዚህ ያለፈው ድርድር ግን የህወሃትን ዕድሜ ከማራዘም የዘለለ ትርጉም እንደማይሰጥ አክለው ተናገረዋል።
“ሕዝብ ላይ የተኮስህ ዕለት አለቀልህ፤ ሕዝብ ላይ መሳሪያ ያነሳህ ዕለት አበቃልህ” እያሉ በንጹሃን ደም ተጨማልቀው በድንገት የተሽቀነጠሩት መለስ ዜናዊ “ውርሳቸው” በደም ግብር እየጸና መሆኑን የሚጠቀሱ በርክተዋል። ስብሃት ነጋም “የመረረው ህዝብ ይነሳል። ይህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ነው” ሲሉ ለቅስቀሳ ፍጆታ ሲደሰኩሩ የተቀዳው ቅጂ በስፋት የማህበራዊ ገጾችን አጨናንቋል። እኒህ ሁለት የህወሃት ካስማዎች እንዲህ መሰሉን ስላቅ እየተጫወቱ ህዝብ ሲጨርሱ እንደነበር አይዘነጋም። በዚህ መልኩ የመቆመሪያ ካርዱን የጨረሰው ህወሃት ካሁን በኋላ ምንም ዓይነት “አስታራቂ ሃሳብ” ቢያመጣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የአንጋሾቹን ምዕራባውያን ቀልብ መሳብ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል የሚለው ብዙዎች የሚጋሩት አመለካከት እየሆነ ሄዷል፡፡
በሌላ በኩል በአማራ ክልል ከተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የክልሉ ኃላፊ የሆኑት ገዱ አንዳርጋቸው ቀለም የማይተፋ ብዕር እንደተሰጣቸው ተነግሯል፡፡ ከሥልጣናቸው ሳይነሱ የፖለቲካ ውሳኔዎችን የመፈረም ሥልጣን ለደመቀ መኮንን መሰጠቱን በህወሃት ወይም በሚዘውረው ሚዲያ በይፋ ባይነገርም በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት ተበትኗል፡፡ በባህርዳር በተደረገው ተቃውሞ የብአዴን ባንዲራ ወርዶ በኢትዮጵያ ሠንደቅ መተካቱ፤ የብአዴን ንብረቶች መውደማቸው፤ ሰሞኑን “ህዝባዊ ወገንተኛ” ሆነዋል እየተባለ የሚነገርላቸው ገዱ ሁልጊዜ በኢህአዴግ ውስጥ “ሁለተኛነት” መጫወት የሰለቸውን ብአዴንን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰዱት ነው በሚል ፍራቻ ውሳኔው እንደተላለፈባቸው ተነግሯል፡፡ ሆኖም በኦሮሚያ ለዘጠኝ ወራት ያህል የኦህዴድ ንብረት ሲቃጠል፣ ሲወድም፣ … ሙክታር ከዲር ከስልጣናቸው ሳይነቃነቁ ገዱ ለዚህ መብቃታቸው ዜናውን ጥርጣሬ ላይ ከመጣል ባለፈ ህወሃትንና አሽከሩን ደመቀን ለበለጠ ጥላቻ በመዳረግ “ገዱ ለምን ተባረረ? ያለግምገማ ለምን ሥልጣኑን ተቀማ? …” በሚሉ አላስፈላጊ ንትርኮች ውስጥ ህዝቡን በማስገባት አቅጣጫ ለማስቀየር ሆን ተብሎ የታቀደ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየትም ተሰጥቶበታል፡፡